Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ በመቆም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 7፣ 2015(ኤፍ ቢ ሲ) ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ለሰላም ዘብ በመቆምና የልማት አጋርነቱን በተግባር በማሳየት የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለጸ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትንሳዔ በዓልን አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ምክር ቤቱ ባስተላለፈው መልዕክት÷የትንሳኤን በዓል ስናከብር ያጡ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና የመረዳዳት ማህበራዊ እሴትን በማጠናከር ሊሆን እንደሚገባ አንስቷል፡፡

ትንሳኤ በሕዝበ ክርስቲያኑ ዘንድ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ረጅሙን የዐቢይ ፆም ወራት በፆም በፀሎት አሳልፈውና ሰሙነ ህማማቱንም በተለያዩ ኃይማኖታዊ ስርዓቶች አልፈው የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በርካታ የውስጥና የውጭ ፈተናዎች እንዳጋጠሟት ጠቅሶ÷ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች በድል እየተሻገረች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት የሚያፋጥኑ አመርቂና ተስፋ ሰጪ ድሎች እያስመዘገበች እንደምትገኝም ጠቁሟል፡፡

በዜጎች መካከል የኢኮኖሚ ልማት ተጠቃሚነትና ማህበራዊ ፍትህ እንዲረጋገጥ፣ ጠንካራ ተቋማት ተገንብተው አስተማማኝ ሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓትን በሀገራችን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድቷል፡፡

በፀጥታና ደህንነት ተቋማት እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ስራዎች የሀገር ግዛት አንድነትንና ሉዓላዊነትን በፅኑ መሰረት ላይ አፅንቶ ለማስቀጠልና ዜጎች በማንኛውም ቦታና ጊዜ ከደህንነት ስጋት ነፃ ሆነው ሰላማዊ ህይወታቸውን በአግባቡ እንዲመሩ ለማስቻል እየተወሰዱ ካሉ የሪፎርም እርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸውም ነው ያለው፡፡

የትንሳኤ በዓል የፍስሃ፣ የሰላም፣ የፍቅርና የመተሳሰብ  ሆኖ እንዲያልፍም ምክር ቤቱ መልካም ምኞቱን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ገልጿል፡፡

Exit mobile version