አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በያዝነው ሣምንት መጨረሻ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የረመዷን ጾም መፍቻ የሆነውን በዓል “ዒድ አልፈጥር”ን ይቀበላል፡፡
“ዒድ አልፈጥር”
“ዒድ አልፈጥር” በዓመት አንድ ጊዜ ከአንድ ወር ጾም እና ጸሎት በኋላ የሚገኝ ከንጥልነት ይልቅ አብሮነትን እየተከለ ለአቅመ ደካሞች ፍስሐን እያስተጋባ የሚከበር የማፍጠሪያ በዓል ነው፡፡
“ዒድ አልፈጥር” የሚል ስያሜ የተሰጠውም የረመዷን ጾምን መቋጨት ተከትሎ የሚፈጠርበት የመጀመሪያ ቀን ስለሆነ ነው ይላሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼኽ ሃሚድ ሙሣ።
“ዒድ አልፈጥር” ማሳሰቢያዎች የሚሰጥበት፣ ምክሮች የሚለገስበት፣ አባት ከልጁ እንዲሁም የሃይማኖት አባቶች ከምዕመናን ጋር በአንድ ቦታ የሚገናኙበት ዓመታዊ እና መለኮታዊ በዓል መሆኑንም ያነሳሉ፡፡
“ዒድ አልፈጥር” ሲከበር . . .
ሙስሊሞች ከሚያከብሯቸው ዓመታዊ በዓላት አንዱ የሆነው “ዒድ አልፈጥር”፥ የራሱ ሕግና ሥርዓት እንዳለው አስተምኅሮቱ ያስረዳል።
ከሕጎቹ አንዱ “ሰላት” መሆኑን ሼኽ ሃሚድ ሙሣ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡
“ሰላቱ አልኢደይን” የሁለት ዒዶች ሰላት (የዒድ አልፈጥር እና ዒድ አልአድሃ) በመባል እንደሚታወቅም ጠቁመዋል፡፡
ስግደቱ የሚከናወነው ከመስጂድ ውጭ በርካታ ምዕመናንን ማስተናገድ በሚችል ቦታ (ሜዳ) መሆን እንዳለበት ይናገራሉ፡፡
በተዘጋጀው ቦታ በሚከናወነው አከባበር ላይ፥ የጾታ፣ ትምህርት፣ ዕድሜ፣ ትዳር እና የሌሎች ሁኔታዎች ገደብ አለመኖሩን አስገንዝበው ምዕመናን መገኘት እደሚጠበቅባቸው አስረድዋል፡፡
ሙስሊሞች ተሰብስበው ዱዓ ሲያደርጉ “ዐሜን” ለማለት፣ “ተክቢራ” ሲደረግ “ተክቢራውን” ለማጀብ እንዲሁም የሙስሊሙ ማሕበረሰብ አካል እንደመሆናቸውም ምዕመናን በአካል መገኘት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።
ምዕመኑ ለስግደት ሲመጣም፥ ከተቻለ አዲስ መልበስ ካልተቻለም ያለውን ንፁህ አድርጎ እንዲለብስ ይመከራል ነው ያሉት።
ምዕመኑ ደስታውን በመግለጽ፣ አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመንከባከብ፣ ዘመድን በመዘየር (በመጎብኘት)፣ የታመሙትን በመጠየቅ፣ ሰውን በማስደሰት በዓሉን ማክበር እንዳለበትም ነው ያመላከቱት።
በጾሙ ወቅት የተሠራውን “ኸይር (መልካም )” ሥራ “ተሃጁዱን”፣ “ተራዊሁን”፣ “ሠደቃውን”፣ “ቂያመለይሉን” እዲሁም ጾሙን ጭምር አላህ እንዲቀበል ዱዓ በማድረግ “ተክቢራ” በማድረግ በዓሉን ማሳለፍ “ሱና” (በሸሪዓ) የተወደደ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
“ዒድ አልፈጥር” ከሌላው “ዒድ” አንጻር
“ዒድ አልፈጥር” ከሌላው “ዒድ” የሚለይበት የራሱ ብቻ ቀለም (መለያ) አለው።
እንደ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ገለጻ፥ “ዒድ አልፈጥር” ን ከሌላው “ዒድ” ከሚለዩት ክንውኖች አንዱ “ዘካተልፊጥር” ነው።
“ዘካተልፊጥር” በ “ዒድ አልፈጥር” ብቻ ስለሚከናወን በዓሉን ከሌላው “ዒድ” እንደሚለየው ነው ዋና ጸሐፊው ያስገነዘቡት።
ስለ “ዘካ”
በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ በየትኛውም ጊዜ አቅመ ደካሞችን አስቦ የሚለገሥ ሥጦታ “ዘካ” ይባላል።
እንደ እስልምና ሃይማኖት አስተምኅሮ የ “ዘካ” ዓይነቶች ሁለት ናቸው። እነሱም፦ “ዘካተልማል” እና “ዘካተልፊጥር” ናቸው።
1. “ዘካተል ፊጥር”
“ዘካተልፊጥር”(የማፍጠሪያ ምጽዋት) በ “ዒድ አልፈጥር” ዋዜማ እና ዕለት ብቻ የሚሰጥ የማፍጠሪያ ስጦታ ነው።
ይች የ “ዘካ” ዓይነት “ነብዩ መሐመድ (ሰለሏህ ዓለይሂ ወሰለም) ከሀገሪቱ ቋሚ ምግብ ተከፍሎ እንዲሰጥ” ያዘዙባት ናት።
ሼኽ ሃሚድ እንዳሉት÷ “ቋሚ ምግብ”ማለት በሀገሪቱ ለምግብነት ከሚያገለግሉ የምግብ ዓይቶች የሚሰጥ ስጦታ ነው፡፡
የሚለገሰውን የእህል መጠን በተመለከተ ሲያብራሩም፥ በአንድ ሰው 2 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም መሆኑን እና ይህም ግዴታ (“ዋጅብ”) ስለመሆኑ በአጽንኦት ይገልጻሉ።
2 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም የ “ዘካተል ፊጥር” መጠን በአንድ ሰው ብቻ ሲሆን÷ የቤተሰብ አባል ቁጥር ሲጨምር የስጦታው መጠንም እንደሚጨምር ነው የሚያስረዱት፡፡
ለምሳሌ፡- አንድ ቤተሰብ ውስጥ ሥድስት የቤተሰብ አባላት ቢኖሩ 6 x 2.5 = 15 ኪሎ ግራም መስጠት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው ብለዋል፡፡
ስጦታውም በተለያየ ምክንያት ለችግር ተጋልጠው በልመና ለሚተዳደሩ ወገኖች ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት።
እነዚህ ወገኖች በ “ዒድ አልፈጥር” እንዲደሰቱ በማሰብ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) “የዛሬን ቀን እንኳን በዓሉን በቤታቸው እንዲያከብሩ፤ እየዞሩ እንዳይለምኑ አድርጓቸው” ብለው አዘዋል፡፡
የነብዩን ትዕዛዝ በመቀበል ምዕመኑ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም እህል እንደሚሰጥም ነው ያስረዱት።
ስጦታው ወደ መስገጃ ቦታ ከሚሄድት ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲሰጠም አስተምኅሮቱ ያዝዛል፡፡
እንደ ሼኽ ሃሚድ ገለጻ፥ ምዕመኑ “ለዒድ ሰላት” ሳይሄድ፣ “ሰላት” ከመሰገዱ በፊት፣ በዋዜማው ወይም በ “ዒድ አልፈጥር” ዕለት ጠዋት ለአቅመ ደካሞች በእህል ማድረስ የግድ ይሆናል፡፡
2. “ዘካተልማል”
“ዘካተልማል” ሁለተኛው የዘካ ዓይነት ነው።
ይህ የ “ዘካ” ዓይነት ባለሃብቶች እና ነጋዴዎች የገንዘባቸውን ዘካ የሚያወጡበት (ምጽዋት የሚሰጡበት) ነው፡፡
በዓመት አንድ ጊዜ ባለሃብቶች እና ነጋዴዎች ካላቸው ሃብት ከ100ው 2 ነጥብ 5 በማሰብ ለሽያጭ (ለገበያ የተዘጋጀን እያንዳንዱ ቁስ እና እንስሳት ጭምር) በብር ቀይረው ዘካ ማውጣት እንደሚጠበቅባቸው ሼኽ ሃሚድ ይገልጻሉ።
ለምሳሌ፦ 100 ሺህ ብር ካፒታል ያለው ሰው 2 ሺህ 500 ብር በዓመት “ዘካ” እንዲያወጣ በ “ሸሪዓ” ግዴታ ተጥሎበታል ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼኽ ሃሚድ ሙሣ፥ ለመላው የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ለ 1 ሺህ 444ኛው ዓመተ ሂጂራ የዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአላህ ራህመት የሚመጣበት፣ የበረካ በዓል እንዲሆን፣ ሀገራችን ከሕዝቦቿ ጋር ሰላም የምትሆንበት፣ የምንፈቃቀርበት፣ የምንዋደድበት፣ የምንተዛዘንበት በዓል እንዲሆን እመኛለሁ ብለዋል በመልዕክታቸው።
ሁሉም ለሁሉም ቋሚ፣ ረዳት፣ አጋዥ እንዲሆንም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆን ምኞቱን ይገ ልጻል፡፡
ዒድ ሙባረክ!!
በዮሐንስ ደርበው
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

