አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በፈረንሳይ የኢኮኖሚ ረዳት ሚኒስትር ከሆኑት ዊሊያም ሩስ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ውይይት ወቅት የተደረሱ በርካታ ስምምነቶችን ሂደት በተመለከተ መክረዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች እዳ ቅነሳን ለማፋጠን በሚወሰዱ ቅድመ ሁኔታዎች ላይም ተወያይተዋል ፡፡
በተጨማሪም÷ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፈረንሳይ ኩባንያዎች በመሰረተ ልማት፣ በመገናኛ፣ በትራንስፖርት፣ በግብርና፣ እንዲሁም በበርካታ የሁለትዮሽ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንቶች ጋር በተያያዘ መክረዋል፡፡
ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ÷ በፈረንሳይ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የቆየ እና የጠበቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እየጠነከረ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱ በርካታ የፈረንሳይ ኩባንያዎች ስኬት በማድነቅ ሚኒስቴሩ የፈረንሳይ ኢንቨስትመንትን በኢትዮጵያ ለማበረታታት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዕዳ ማሻሻያ እና የኦፊሻል አበዳሪዎች ኮሚቴ (ኦሲሲ) እንዲቋቋም ጥያቄ ማቅረቧን ተከትሎ ፈረንሳይ እና የቻይና ሕዝብ ሪፐብሊክ በተሳካ ሁኔታ ለኢትዮጵያ የአበዳሪዎች ኮሚቴ ማቋቋማቸው የሚታወስ ነው።
ዊሊያም ሩስ በበኩላቸው÷ስለ ኦሲሲ የስራ እንቅስቃሴ እና ከሰፊው የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ፕሮግራም ጋር በተጣጣመ መልኩ የፋይናንስ ዋስትና ለመስጠት በሁሉም አበዳሪዎች ስለ ሚታየው ቁርጠኝነት ለሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያን የዕዳ ማሻሻያ ጥያቄም በአፋጣኝ ለመፍታት ቁርጠኝነት መኖሩን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

