አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ጋር በተያያዘ ሕጋዊ መስመር መዘርጋቱን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ከውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል ።
በመግለጫቸውም ከሊባኖስ መንግስት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ወደ ሀገሪቱ ገብተው መሥራት እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡
በዚህም የሊባኖስ መንግስት ከአሰሪዎች አያያዝ፣ ከሰራተኞች ደመወዝ እና ደኅንነትን ከመጠበቅ አንጻር ክትትል ያደርጋል ነው ያሉት፡፡
የዜጎችን ደኅንነት እና ተጠቃሚነት የሚያስጠብቅ ስምምነት መደረጉንም አመላክተዋል፡፡
በተመሳሳይ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት ጋር ውይይት ተደርጎ የደመወዝ፣ የዜጎች መብት እና ደኅንነትን የሚያስጠብቅ ማሻሻያ ለማድረግ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል ።
አንድ ሰው ለሥራ ሁለት ዓመታትን የኮንትራት ውል የሚፈራረም ሲሆን÷ ካልተመቻቸው በሕጋዊ መንገድ የመቀየር መብት እንዳላቸው ነው የገለጹት፡፡
በከፊል የሰለጠኑ እና ሙሉ በሙሉ የሰለጠኑ ወንዶች እና ሴቶች በሀገራቱ መስራት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ከሚሰሩበት ቤት መጥፋት ግን ወንጀል መሆኑን ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡
ቀደም ሲል በነበሩ ዓመታት በሥራ ስምሪት ሂደቱ የግለሰቦች መልካም ፈቃድ የጎላ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ግን ሀገራት በሚያደርጉት ንግግር እና ስምምነት ብቻ መፍትሄዎች እንደሚቀመጡ አረጋግጠዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ

