Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በደቡብ ክልል የሚከሰትን ድርቅ በዘላቂነት መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ድርቅ በተደጋጋሚ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደር ቢሮ አስታወቃ።

በአፍሪካ ቀንድ የምግብና ስርዓተ ምግብ ደህንነት ፕሮጀክት (ብሪፎንስ) እና የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ (ድራይቭ) የተሰኙ ፕሮጀክቶች ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን ቱርሚ ከተማ ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የደቡብ ክልል አርብቶ አደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎሬ ካኩታ እንዳሉት÷ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ የሚቋቋም ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ ነው።

ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተተገበሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለአብነት በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ሁለት ወረዳዎችና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አምስት ወረዳዎች ድርቅን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በእነዚህ አከባቢዎች በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) አስተባባሪነት ከአፍሪካ ልማት ባንክ እና ከኢትዮጵያ መንግስት በተገኘ ፈንድ 9 የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶች፣ 86 አነስተኛ የውሃ ተቋማት መገንባታቸውን አንስተዋል፡፡

32 ተበላሽተው የነበሩ የውሃ ተቋማት እድሳት ተደርጎላቸው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉንም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች፣ የእንስሳት መኖ፣ የገበያ ማዕከላትና ላብራቶሪ የማቋቋም ስራዎች እንዲሁም የአርብቶ አደር ሴቶችንና ወጣቶችን የኢኮኖሚ አቅም የማሳደግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል ዛሬ የተጀመሩት ፕሮጀክቶችም ድርቅን መቋቋምና ለአደጋዎች የማይበገር ጠንካራ ማህበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳና በሙከራ ደረጃ ተተግብሮ ውጤታማ የሆነው የእንስሳት ኢንሹራንስ ለአርብቶ አደሩ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ እንደታየም ተናግረዋል።

ሌላው የአደጋ ስጋት ቅነሳና አካታች የኢኮኖሚ እሴት ማሻሻያ (ድራይቭ) ፕሮጀክት በሐመር፣ ሳላማጎ፣ ኛንጋቶም፣ ማሌ፣ በናፀማይ እና ዳሰነች ወረዳዎች እንደሚተገበር ኢዜአ ዘግቧል።

በአካባቢው በመኖ ልማትና ሌሎች የኢንቨስትመንት ሥራ ላይ የተሰማሩ ልማታዊ ባለሃብቶችም 40 በመቶ ቆጥበው ብድር የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ተገልጿል።

Exit mobile version