Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል የሥራ እንቅስቃሴን በመገደብ ኢኮኖሚ እንዲደቅ የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ ይገባል – የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ እንቅስቃሴን በመገደብ የክልሉ ኢኮኖሚ እንዲደቅ እና የሕዝቡ ኑሮ እንዲጎሳቆል የሚጥሩ አካላት ሊታረሙ እንደሚገባ የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው የአማራ ክልል ወቅታዊ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም  የትንሣዔ እና የዒድ አልፈጥር በዓላት በሰላም መጠናቀቃቸውን ጠቅሰው÷ የክልሉ ወጣቶች እና መላው ማኅበረሰብ ለሰላም የነበረው ተሳትፎ የሚደነቅ ነበር ብለዋል።

የክልል ልዩ ሃይሎችን መልሶ የማቋቋም እና የማደራጀት ሥራ ለማደናቀፍ ሲወራ የቆየው አሉባልታ ለሀገር ውለታ የከፈሉ የአማራ ልዩ ሃይል አባላትን ክብር የሚመጥን አልነበረም ሲሉም ገልጸዋል።

ልዩ ሃይሉ ትጥቁን ፈትቶ እና ጥቅሙ ሳይከበርለት ሊበተን እንደሆነ በማስመሰል አባላቱ ወደ ታለመው ቀጣይ ተልዕኮ እንዳይሰማራ የሴራ ቅስቀሳ ተደርጓል ነው ያሉት።

በዚህም የተነሳ ያልተገባ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው÷የአማራ ልዩ ሃይል በተሠራበት አሉባልታ ልክ ያልተገኘ እና ይልቁንም ሴረኞችን ወደ ኃላ በመተው ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ቅድሚያ የሰጠ በመሆኑ ታሪካዊ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

አሁን ላይ አብዛኛው የልዩ ሃይል አባላት መብታቸው እና ጥቅማቸው ተከብሮላቸው እና አጫጭር ስልጠናዎችን ወስደው ወደ ተመደቡባቸው ተቋማት በመግባት ላይ እንደሚገኙም ጠቅሰዋል።

አሁን ያለው የክልሉ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ በአንጻራዊነት ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷ይሁን እንጅ የሕዝቡን የሰላም እርካታ ለማምጣት በርካታ ሥራዎች ይቀራሉ ብለዋል።

ኅብረተሰቡ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ መንግሥት ሰላምና ጸጥታን የማስጠበቅ መደበኛ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡም ተፈላጊ የሆነውን ሰላም ለማምጣት መጣር እና ችግሮች ሲፈጠሩም በወያየት መፍታት አለበት ብለዋል።

ሕዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር የሚያደርጉ አካላት ተገቢውን እርማት እንዲያገኙ የፌደራልና የክልል የጸጥታ ተቋማት በቅንጅት እየሠሩ መሆኑም ተገልጿል።

ቀጠሮ እየያዙ በየጊዜው መንገድ በመዝጋት እና የተቋማትን ሥራ በማስተጓጎል ሕዝብን ረፍት ለመንሳት በሚጥሩ አካላት ላይ ተገቢው እርምጃ እንደሚወሰድም አቶ ደሳለኝ ገልጸዋል።

ሕዝቡ እነዚህን አካላት በማጋለጥ እና ለጸጥታ ተቋማት በመጠቆም በተረጋጋ መልኩ እና በሙሉ አቅሙ ወደ ልማቱ እንዲዞርም መልዕክት ማስተላለፋቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

 

 

 

 

 

Exit mobile version