Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሐይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል እየተሰራ ነው – አቶ ታዬ ደንደአ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ ተናገሩ፡፡

የሰላም ሚነስቴር ከኦሮሚያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር ”የሃይማኖት አስተምህሮ ለሰላም ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ በክልሉ የሚገኙ የሐይማኖት አባቶች እና ከሰላም እና ፀጥታ ቢሮ የተወጣጡ አባላት በተገኙበት ወይይት አካሂዷል ።

በመድረኩ በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ታዬ ደንደአ÷ ሁሉም ሃይማኖቶች ስለ ሰላም ፣መከባበርና አንድነት የሚያስተምሩ ቢሆኑም በሀገራችን ሐይማኖትን ሽፉን ያደረጉ ግጭቶች ለሰላም መደፍረስ እንደ አንድ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር የሐይማኖት ተቋማት በውስጣቸው የሚከሰቱ ችግሮችን በራሳቸው እንዲፈቱ እና በሐይማኖቶች መካከል መከባበር እንዲኖር በትኩረት እየሰራ እንደሆነም አቶ ታዬ መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡፡፡

በተጨማሪም ÷የሐይማኖት ተቋማትና መንግሥት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሰሩ እና የሐይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ ሚናቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እየሰራን ነው ብለዋለል፡፡

የኦሮሚያ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ተወካይ አቶ ታመነ ሳህሉ በበኩላቸው÷ የሐይማኖት ተቋማት ለሰላም ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመረዳት በክልሉ ከሚገኙ የሐይማኖት ተቋማት ጋር በሰላም ዙሪያ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

Exit mobile version