አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነቱን ለማጽናት በርካታ የሚደነቁ ተግባራትን አከናውናለች ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ሰርዋ ቴቴ ተናገሩ፡፡
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በሒደቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ‘ጦርነት ይብቃ፤ ሰላምን እናጽና’ በሚል መሪ ቃል የእውቅና እና ምስጋና መርሐግብር ትናንት በአዲስ አበባ ተከናውኗል።
በመርሐ ግብሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሃና ሰርዋ ቴቴን ጨምሮ ለሰላም ስምምነቱ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
ልዩ መልዕክተኛዋ ሃና ሰርዋ ቴቴ÷ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ተከስቶ የነበረው ጦርነት በሰላም ስምምነት የተቋጨበት መንገድ አድንቀዋል፡፡
በፕሪቶሪያ ከተፈረመው ስምምነት ወዲህ በርካታ ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን ጠቅሰው÷ ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
ዘላቂ ሰላም በአንድ ቀን ሊመጣ እንደማይችል የተናገሩት ልዩ መልዕክተኛዋ÷ ከዚህ አኳያ የሰላም ስምምነቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች በአቀራረበ መልኩ እንዲጸና በየእለቱ መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የሰላም ስምምነቱን በመተግበር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት እጅግ እንዳስደሰታቸውም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በቀጣይ ሰላማቸውን አስጠብቀው ሀገራቸውን በጋራ በመገንባት ለአፍሪካዊያን አብነት እንደሚሆኑም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

