አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) “በፍርድ ቤት የተያዘ የሙስና ክስን እንዲቋረጥ አስደርጋለሁ” በማለት ጉቦ ተቀብሏል በተባለ ግለሰብ ላይ ክስ ተመሰረተ፡፡
ክሱ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።
ተከሳሽ ሳሙኤል ታደሰ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 ነዋሪ መሆኑ እና በግል ሥራ ላይ መሰማራቱን በፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የቀረበው ክስ አመላክቷል፡፡
ተከሳሹ በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ብቻ ሊሰጥ የሚገባውን ልዩ መብት ወይም ጥቅም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ÷ በሙስና ወንጀል ተከሶ ጉዳዩ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ችሎት እየታየ የሚገኝ ተከሳሽን “ክስ እንዲቋረጥ አስደርጋለሁ” በማለት ከተከሳሽ ቤተሰቦች ጉቦ መጠየቁ በክሱ ተገልጿል፡፡
በየካቲት ወር 2015 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ጎንደር ሆቴል ውስጥ ከ1ኛና 2ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የግል ተበዳዮች ጋር በመገናኘት እምነት ለማግኘት አስቦ በሐሰት ዐቃቤ ሕጎችንና የፍትሕ ሚኒስቴር ኃላፊዎችን እንደሚያውቃቸው በመግለጽ÷ “ክሱ እንዲቋረጥና ተከሳሹ ከስር እንዲፈታ አደርጋለሁ” በማለት ለማስፈጸሚያ 2 ሚሊየን ብር ጉቦ እንዲሰጡት መጠየቁን ክሱ አመላክቷል፡፡
በግል ተበዳይ የሆነውን 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ይዞ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ቢሮ በመሄድና ኃላፊውን እንደሚያውቀው በማስመሰል በግል ተበዳይ በኩል እምነት እንዲጣልበት መሞከሩን ክሱ ያስረዳል፡፡
እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ 22 አካባቢ ከዚሁ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ጉዳይ ለማስፈጸሚያ 2 ሚሊየን ብር እንዲያመጣ ከዚህም ውስጥ ቅድሚያ ክፍያ 350 ሺህ ብር እንዲሰጠው መጠየቁ በክሱ ተጠቅሷል፡፡
በዚህ መነሻ÷ የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም 42 ሺህ ብር፣ የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም 100 ሺህ ብር እንዲሁም የካቲት 24 ቀን 2015 ዓ.ም 40 ሺህ ብር በተለያዩ ሰዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ የሒሳብ ቁጥር ገቢ እንዲደረግለት ማስደረጉም ነው የተመለከተው፡፡
በመቀጠልም የበለጠ በሐሰት ታማኝነት ለማግኘት በማሰብ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አካባቢ የግል ተበዳይ 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክርን ይዞ በመሔድ ከፍተኛ ኃላፊዎችን እንደሚያውቅ ለማስመሰል ጥረት አድርጓልም ነው የተባለው፡፡
ሠነዶችን በዐቃቤ ሕግ ቢሮ እንዳስገባ በማስመሰል ጉዳዩ ለውሳኔ እንዲቀርብ ተጨማሪ 150 ሺህ ብር በመጠየቅ መጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ደሳለኝ ሆቴል 1ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ማለትም የግል ተበዳይ ገንዘቡን ይዞ እንዲመጣ በመንገር 80 ሺህ ብር በቼክ 50 ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ከግል ተበዳይ ተቀብሎ ሊያመልጥ ሲል በቁጥጥር ስር መዋሉ በክሱ ተገልጿል።
በዚህም የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 29 (1) ስር የተደነገገውን በመተላለፍ በግል ተሰሚነት መንገድ የሙስና ወንጀል መፈጸም በሚል ተከሷል።
ተከሳሹ ክሱ ከደረሰው በኋላ በጠበቃው አማካኝነት የዋስትና መብቱ እንዲጠበቅ ባቀረቡት ጥያቄ ላይ ከከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ጋር ክርክር ተደርጎበታል።
የግራ ቀኝ ክርክሩን የተከታተለው ችሎቱ በዋስትናው ላይ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሚያዝያ18 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ

