አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገርን ጥሪ ተቀብለው ተልዕኳቸውን በድል ላጠናቀቁ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የሽኝትና የምስጋና መርሐ ግብር ተካሂዷል።
የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ወታደራዊ አማካሪና የሜካናይዝድ አስተባባሪ ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌ/ጄ አለምእሸት ደግፌ÷ የሠራዊት አባላቱ በሀገር ላይ ያጋጠሙ አደጋዎችን በመቀልበስ ህዝብና መንግስት የማይረሳው አኩሪ ሀገራዊ ገድል መፈፀማቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሠላምና መረጋጋት የሠራዊት አባላቱ በግንባር በመሰለፍ ያደረጉት ተጋድሎ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አባላቱ ተሞክሯቸውን ለተተኪ የሠራዊት አባላት በማካፈል ጠንካራ ዲሲፕሊንና የሀገር ፍቅርን በማላበስ ጉልህ አሥተዋፅኦ ማበርከታቸንም ገልፀዋል።
የመከላከያ ሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ሃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሃጫሉ ሸለመ በበኩላቸው÷ የሠራዊት አባላቱ ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም በተለያየ ጊዜ ያጋጠሙ ጠላቶችን ድባቅ በመምታት አይበገሬነታቸውን አስመስክረዋል ብለዋል፡፡
በክብር የተሸኙት የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላቱ በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ ሠላምን በማጽናት ረገድ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው ሌተናል ጄኔራል ሃጫሉ አሳስበዋል።
ሽኝት የተደረገላቸው የሠራዊት አባላት የሀገርን ጥሪ ተቀብለው ሠላምና አንድነትን ለማረጋገጥ በከፈሉት ዋጋ ኩራት እንደተሰማቸውም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በማንኛውም ሁኔታ ሀገራቸውን በሚችሉት ሁሉ ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጣቸውንም የመከላከያ ሰራዊት መረጃ ያመላክታል፡፡

