አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት ያሳየው የሰላም ቀናኢነት አዲስ የፖለቲካ ባህል በኢትዮጵያ ለማዳበር መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን ተናገሩ፡፡
ችግሮችን ከግጭት ይልቅ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መሞከሩ ለኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ የሚሰጡ ናቸው ነው ያሉት ምሁራኑ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት በወላይታ ሶዶና በዋቸሞ ዩኒቨርስቲዎች የአፍሪካ ጉዳዮች መምህርና ተመራማሪዎቹ ንጋቱ አበበ እና በቀለ ሃብታሙ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግና ወደ ሀሳብ ፖለቲካ የሚወስድ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና በብዙ ፍላጎቶች የተወጠረ ነው ያሉት ምሁራኑ በውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች የውጭ ተጋላጭነትን ስለሚጨምሩ የማይቻለውን በሃይል ፍላጎትን ለማሳካት የሚደረጉ ጥረቶች መቋጨት አለባቸው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በጦርነት የሚደርሰውን ውድመት በበቂ ሁኔታ አይታለች ያሉት ምሁራኑ የተጀመረውን የሰላም መንገድ ለማፅናት ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በአፈወርቅ እያዩ

