አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ትምህርት ዘርፎች በትብብር እየሰሩ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ይቭጊኔ ተርኺንተናገሩ፡፡
አምባሳደሩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት÷ኢትዮጵያና ሩሲያ በህዋ ሳይንስ ጥናትና ምርምር፣ በኒውክሌር ሃይል አጠቃቀም፣ በስነ ህይዎት ጥናት እና በሌሎች ዘርፎች በትብብር እየሰሩ ነው።
በተለይም በስነ ህይዎት ጥናት ዘርፍ ሀገራቱ ለ40 ዓመታት በጋራ ሲሰሩ እንደነበር ያስታወሱት አምባሳደሩ÷በተደረጉ የስነ ህይዎት ምርምሮችም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በቅርቡ ሞስኮ በኢትዮጵያ የስነ ህይወት ጥናት ማዕከል ለማቋቋም ማቀዷን እና ማዕከሉን ለመገንባት የሚያስችል የስምምነት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2019 ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በኒውክሌር ኃይል አጠቃቀም ስምምነት መፈራረማቸውን እና በዘርፉ ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል፡፡
ይህ ስምምነትም ኢትዮጵያ በሕክምና፣ በግብርና እና ሌሎች ዘርፎች እያከናወነች ያለችውን እንቅስቃሴ እንድታፋጥን መልካም እድል እየሚፈጥር መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡
የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትብብርን ለማጠናከር በሩሲያ ፌዴሬሽን እና በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በወንደሰን አረጋኸኝ

