አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሰለጠነ የሰው ኃይል ለደቡብ ኮሪያ የሥራ ገበያ ለማቅረብ ኢትዮጵያ ዋነኛ ተመራጭ መዳረሻቸው መሆኗን የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዎኪሂ አስታወቁ፡፡
የስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ ከደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዎኪሂ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ÷ የትብብር ማዕቀፎችን ለማጠናከር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በሰፊው መወያየታቸውን ሚኒስትሯ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡
የወጣቱን የፈጠራ ችሎታ ለማሳደግ የሚያስችሉ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን ከደቡብ ኮሪያ ልምድ በመውሰድ በትብብር ለመስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም መወያየታቸውን ነው ሚኒስትሯ ያነሱት፡፡
ወደ ኮሪያ የሰለጠነ የሰው ሃይል መላክን ጨምሮ የትብብር መስኮችን በማስፋት በጋራ ለመስራት የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ከፍተኛ ፍላጎትም ሚኒስትሯ ለአምባሳደሩ አስረድተዋል::
የደቡብ ኮሪያው አምባሳደር ካንግ ሲዎኪሂ በበኩላቸው ÷ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በቀድሞው ጊዜ ከደቡብ ኮሪያ ህዝብ ጎን ቆመው ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሁልጊዜም በባለውለታነት በማስታወስ በደቡብ ኮሪያ ህዝብና መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል::
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፉን በማዘመን የበቁ ባለሙያዎችን አፍርቶ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የተጀመረውን የሪፎርም ስራ እንደሚደግፉም አምባሳደሩ ገልጸዋል::
የሰለጠነ የሰው ኃይል ለደቡብ ኮሪያ የሥራ ገበያ በማቅረብ ረገድም ኢትዮጵያ ዋነኛ ተመራጭ መዳረሻቸው መሆኗን እንዲሁም በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ጥያቄው የቀረበላት ሀገር መሆኗን ነው የጠቀሱት::

