Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

አቶ ርስቱ ይርዳ በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳ በአማራ ክልል ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማቸውን ሃዘን ገልጸዋል፡፡

አቶ ርስቱ ይርዳ በሃዘን መግለጫቸው ÷አክራሪ ሀይሎች ታላቅ የህዝብ አደራን ተቀብለው በጀግንነት እና በታታሪነት ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በቅንነት ሲያገለግሉ የነበሩትን መሪ እንድናጣ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።

አሁን ባለንበት ዘመን ልዩነት በምክክር እና በውይይት መፍታት ሲቻል የመሳሪያ አፈ ሙዝን በመፍትሄነት መጠቀም ተስፋ ቢስነትን ያመላክታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ÷ ጀግናችንን በሞት ብንነጠቅም እንደ ሀገር የጀመርነው የልማትና የእድገት ጉዞ ላፍታም ሊገታ አይችልም ነው ያሉት።

አክራሪ ሃይሎች በአቋራጭ ስልጣን ለመያዝ ያልፈነቀሉት ድንጋይ እንደሌለ ጠቁመው÷ መግደልን አማራጭ ማድረጋቸው ምን ያህል በህዝብ ደም የመነገድ ፍላጎት እንዳላቸው ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል።

አቶ ግርማ የሺጥላ በስራ ክቡርነት የሚያምኑ የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ በብቃት እተወጡ የነበሩ ጠንካራ አመራር መሆናቸውንም በሀዘን መግለጫቸው ገልጸዋል።

ለቤተሰቦቻቸው፣ ለወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ ለስራ ባልደረቦቻቸው፣ለትግል አጋሮቻቸው እንዲሁም ለመላው ህዝብም መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

በተመሳሳይ የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የፓርቲው የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈ ቤት ኃላፊ በአቶ ግርማ የሺጥላ ህልፈተ ሞት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።

አቶ ግርማ የሺጥላ ለህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊ አንድነት በፅናት የሚታገሉ፣ ህዝቦችን በእኩልነት መርህ የሚመለከት ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ግምባታ ኢትዮጵያ ዛሬ ከሚያስፈልጓት የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ ነበሩ ብሏል ፓርቲው።

ለለወጥ፣ ለእውነትና ለዴሞክራሲ ግንባታ በአጠቃላይ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ካለው ፅኑ አቋም በመነጨ ብርቱ ትግል የሚያደርጉ ግልፀኛ ታጋይ ነበሩ ሲልም አውስቷል፡፡

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ለአቶ ግርማ የሺጥላ መላ ቤተሰቦች እና ባልደረቦቻቸው መፅናናትን ተመኝቷል፡፡

 

 

 

Exit mobile version