አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በአማራ ክልል ብልጽግና ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ግርማ የሺጥላ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን ገልጿል፡፡
የሲዳማ ክልል በሀዘን መግለጫው÷የጥፋትን መንገድን በተከተሉ የሐገርን ሉዓላዊነት ክብር ለማዋረድ ሌት ተቀን የሚዳክሩ ኃይሎች ቅንጣት ታክል ትግላችንንና ሰላማችንን አይቀለበስም ብሏል።
እነዚህ ኃይሎች በሰለጠነ መንገድ ፖለቲካዊ አካሔዳቸውን ማስፈፀም የማይችሉና ሁል ጊዜ ፀብና ግጭት በመፍጠር አጀንዳቸውን ለማስፈፀም ነፍጥ የሚያነሱ ከዘመኑ ፖለቲካ ስልጣኔ አንፃር ችግሮቻቸውን በውይይት ለመፍታት አቅም የሌላቸው ናቸው ሲል ገልጿል፡፡
የህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ከፍታና አንድነት ለመናድ የሚታትሩ የሀገር ጠላቶች ናቸውም ነው ያለው።
እነዚህ ኃይሎች በፈፀሙት የወንጀል ድርጊት መላው የክልላችን ሕዝብና መንግሥት የተፈጠረውን አስነዋሪና አፀያፊ ድርጊት ከማውገዝ ባሻገር ወንጀለኞች ለሕግ ቀርበው ፍትህ እስኪረጋገጥ ድረስ ከወንድ አማራ ህዝብና መንግሥት ጎን እንደሚቆም የክልሉ መንግሥት ያረጋግጣልም ብሏል፡፡
የሲዳማ ክልል ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆቻቸው፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው እንዲሁም ለመላው አማራ ሕዝብ የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገልጿል፡፡

