አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በግርማ የሺጥላ ላይ በደረሰው አሰቃቂ ግድያ የተሰማውን ሐዘን ገለጸ፡፡
ምክር ቤቱ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው የሐዘን መግለጫ÷ አቶ ግርማ የሺጥላ ለሕዝባቸው መሻሻል እና ለክልላቸው ልማት፣ ብሎም ለሀገሪቱ ዕድገት የበኩላቸውን ሲወጡ ኖረዋል ብሏል።
የአመለካከት ልዩነቶችን እና ስብራቶችን እርስ በርስ በመገዳደል ለውጥ ማምጣትና ማስተካከል እንደማይቻልም ነው ምክር ቤቱ የገለጸው፡፡
ሥር የሰደዱ ግጭቶች እንኳን ቢሆኑ በአመጽ ሳይሆን በመነጋገር፣ በመወያየት፣ በመግባባትና በመደማመጥ እንዲሁም በመተባበር ብቻ መፈታት ይኖርባቸዋል ነው ያለው በመግለጫው፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ድርጊቱን በጽኑ እንደሚያወግዝ ገልጾ÷ መንግስት ይህን አስነዋሪ ተግባር የፈጸሙ አካላትን በአፋጣኝ በቁጥጥር ስር በማዋል ተገቢውን የሕግ ተጠያቂነት እንዲያረጋግጥ ጠይቋል፡፡
ምክር ቤቱ በግርማ የሺጥላ ግድያ የተሰማውን ሐዘን በመግለጽ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ለአማራ ክልል መንግስትና ሕዝብ እንዲሁም ለቤተሰቦቹ እና ወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን ተመኝቷል፡፡