አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥበቃ ሰራተኛን በማፈን እና የመጋዘን በር ሰብረው በመግባት 78 ቴሌቪዥኖችን ሰርቀው የተሰወሩ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ወንጀሉ የተፈፀመው ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው በተለምዶ ሩታ ጀርባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው።
በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የካራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ እንደተናገሩት ÷ግለሰቦቹ በቡድን ተደራጅተውና ጨለማን ተገን አድርገው ከለሊቱ 7 ስዓት ከ40 ደቂቃ ገደማ በመኪና ወደ አንድ ግለሰብ የኤሌክትሮኒክስ እቃ ማከማቻ መጋዘን መሄዳቸውን ይናገራሉ፡፡
በመቀጠልም የጥበቃ ሠራተኛውን አፍነው ከደበደቡትና የመጋዘኑን በር ሰብረው ከገቡ በኋላ “ስማርት ጂ ጎግል ” የሚል ስያሜ ያላቸው ባለ 32 ኢንች ብዛት 78 ቴሌቪዥኖችን ሰርቀው መሰወራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።
የግል ተበዳይም ንብረታቸው እንደተሰረቀ ወዲያውኑ ለካራ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ባቀረቡት አቤቱታ መሰረት ፖሊስም የምርመራና የክትትል ቡድን በማቋቋም ከፍተኛ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
በዚህም ÷ በወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳትፎ ያላቸውንና ግብራበሮቻቸውን በአጠቃላይ ዘጠኝ ተጠርጣሪዎችን ወንጀሉ በተፈፀመ በሦስት ቀናት ውስጥ በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ኮማንደር አበባው ዳምጤ አስረድተዋል፡፡
100 ሺህ ብር በተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ በመገኘቱ በኤግዚቢትነት ተይዞ የምርመራ ስራው መቀጠሉንና ተጠርጣሪዎቹን በመያዝ ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ እንደነበርም ነው ኃላፊው የጠቀሱት፡፡
በተለይም በለሊቱ ጊዜ የፖሊስ አባላት የጥበቃ ሰራተኞችን በማንቃት የሚያከናውኑትን ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግና ጨለማን ተገን በማድረግ የሚፈፅሙ ወንጀሎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡

