Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኢትዮጵያ ግብርናና ኢነርጂ ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው የእንግሊዝና ቱርክ ኩባንያዎች አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 21 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የእንግሊዝና ቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በግብርና እና ኢነርጂ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ከሚያዚያ 18 እስከ 20/ 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢንቨስትመንት ፎረም በርካታ የውጭ ሀገራት ኩባንያ ኃላፊዎች፣ ተወካዮችና ሌሎች የዘርፉ አካላት መሳተፋቸው ይታወቃል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በርካታ የውጭ ሀገር ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት ወስነው የመግባቢያ ስምምነት ፈጽመዋል።

በፎረሙ የተሳተፉ ሌሎች የውጭ ኩባንያዎችም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ በግብርናና ኢነርጂ ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውና ፎረሙ ኢትዮጵያ ያላትን የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመለየት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

ከእነዚህ ባለሃብቶች መካከል በግብርና ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰራው የእንግሊዝ “ኢኮሲስተም” የተሰኘ ኩባንያ አንዱ ነው።

የኩባንያው የቢዝነስ ዳይሬክተር ፊል ጋፍኒይ ኢትዮጵያ ግብርናን ጨምሮ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ያሏት ሀገር መሆኗን በፎረሙ መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

ፎረሙ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ፖሊሲና መንግሥት ለኢንቨስተሮች የሚሰጣቸውን ማበረታቻዎችና ድጋፍ እንዲያውቁ አስችሏልም ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም በቀጣይ በሀገር ውስጥ አብረው የሚሰሩ አጋር ድርጅት በመፈለግ በግብርናው ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

በማዕድን፣ ኮንስትራክሽንና ኢነርጂ ሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩት ግዙፍ ኩባንያዎችን የሚመሩት የቱርክ ባለሀብት ሙሃመድ ሲፍትሲ በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ በማዕድን፣ ኢነርጂና በሌሎች ኢንቨስትመንት አማራጮች እምቅ አቅም እንዳላት ለማወቅ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም÷ ሀገሪቱ ካላት የኢንቨስትመንት አማራጭ ውስጥ በኢነርጂ ዘርፍ የ50 ሚሊየን ዶላር ካፒታል ያለው ኢንቨስትመንት ለማካሄድ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሌላው በግብርና እና በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማራው “ኤም ኤች ኤ ማሺንታየር ሁድሰን” የተሰኘ የእንግሊዝ ኩባንያ አጋር ማርክ ሉምስደን ÷ ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ይህንንም ተከትሎ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የኢንቨስትመንት አማራጭ ዓለም አቀፍ ባለኃብቶች መዳረሻ ሊያደርጓት የሚችል ሀገር መሆኗን ባለሀብቶቹ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version