አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደብረ ማርቆስ ከተማ የተከመረ ኮንክሪት ፖል ላይ ሲጫወቱ ከነበሩ አምስት ህጻናት ውስጥ ፖሉ ተንከባሎ የሁለት ሕጻናት ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
ለህልፈት የተዳረጉትም የ15 እና16 ዓመት ዕድሜ ህጻናትመሆናቸውን የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር የ1ኛ ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ ኮማንደር ጌትነት መስፍን ተናግረዋል ፡፡
በተጨማሪም ስድስት ፣ስምንት እና አስር ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሶስት ሕጻናት በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸው በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
ኮማንደር ጌትነት ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ፖል እና መሠል አገልግሎት የሚሰጡ ግብዓቶች ላይ ህጻናት እንዳይጫወቱ የማድረግ ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በየአካባቢው ጉዳት የሚያደርሱ ነገሮችን ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ እንዲቀመጥ ማድረግ እንደሚገባ መጠቆማቸውንም የከተማዋ ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

