Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመተከል ዞን ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪን ተቀብለው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላምን አማራጭ በመቀበል ወደ ቀደመ ሕይወታቸው ተመልሰዋል፡፡
 
ታጣቂዎቹ በጦርነትና ግጭት ከመጠፋፋት ውጭ ምንም አይነት መፍትሄ አለመኖሩን በመረዳት መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ነው ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው የተመለሱት፡፡
 
በዞኑ ውስጥ በዳንጉርና ጉባ ወረዳዎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ነበሩበት ሲመለሱ የግልገል በለስ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውላቸዋል።
 
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ለሜሳ ዋውያ ÷ መንግስት ያቀረበውን የሰላምን አማራጭ በመጠቀም ወደ ቀደመ ሕይወታቸው የተመለሱ ወገኖችን አመስግነዋል፡፡
 
መንግስት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ባለፈ በቀጠናው ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ወደ ልማት ለመግባት ያቀረበውን ሰላም በመቀበል ለተመለሱ አካላት ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲገቡ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
 
እነዚህን አካላት ወደ ሰላም ለመመለስ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት በተጨማሪ የሀገር ሽማግሌዎች ጉልህ ሚና እንደተጫወቱ መገለጹንም የዞኑ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።
Exit mobile version