Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በኦሮሚያ ክልል የነዳጅ ግብይትን በዲጂታል ለማድረግ ዝግጅት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የነዳጅ ግብይቱን ሙሉ በሙሉ በዲጅታል ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ገሾ ዛሬ በሰጠው መግለጫ÷ በክልሉ ከነገ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ብቻ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስና በማንዋል (በጥሬ ገንዘብ) ይሰጣል ብሏል፡፡

ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ግን ግብይቱ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ብቻ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

ለዚህም ከኢትዮ ቴሌኮም እና ከተለያዩ ባንኮች ጋር አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ነው ቢሮው ያስታወቀው፡፡

በኩፖን የሚጠቀሙ ተቋማት ከሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኩፖን መጠቀም እንደማይችሉ እና ቀድመው ዝግጅት እንዲያደርጉም ቢሮው አሳስቧል።

በዙፋን ካሳሁን እና በሳሙኤል ወርቃየሁ

Exit mobile version