Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ ቦምቦችን ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የ12 ቀን ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 25 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ 10 ቦምቦችን በቤት ውስጥ ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ የ 12 ቀን ጊዜ ፈቀደ።

ህገ መንግስቱንና ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለማፍረስ በኢ- መደበኛ አደረጃጀት ተደራጅተው በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ ከአማራ ክልል  10 ቦምቦችን በማምጣት በየካ ክፍለ ከተማ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት ውስጥ ቦምቦችን ደብቀው ተይዘዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ነው ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው ለፖሊስ  የ12 ቀን ጊዜ የተፈቀደው።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በትናንትናው ዕለት ክርክር በተካሄደባቸው ሁለት የጊዜ ቀጠሮ መዝገቦች ተመልክቶ ዛሬ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግባቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን መርማሪ በአዲስ አበባ ከተማ ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት፣ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም በማሰብ በተከራዩበት መኖሪያ ቤት 10 ቦምቦችን ደብቀው የተያዙ ሞላልኝ ሲሳይ እና አብርሃም ጌትነት በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ውስጥ የምስክሮችን ቃል መቀበሉ እንዲሁም ከተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ጋር የተያያዙ በርካታ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን የተጠርጣሪዎችንም ቃል መቀበሉን ለችሎቱ አስረድቶ ነበር ።

በሁለተኛው መዝገብ ደግሞ ማለትም በአማራ ክልል አመፅ፣ በሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ፣ አንዱ ህዝብ በአንዱ ህዝብ ላይ መተማመን እንዳይኖረው ለመከፋፈል ሲሰሩ ነበሩ ተብለው የተጠረጠሩ ሰይፈ ተስፋዬ፣ ማስረሻ እንየው፣ ጌታቸው ወርቄ፣ አንደበት ተሻገር፣ ታደሰ ወዳይነው በተባሉ 5 ተጠርጣሪዎች ላይ ከዚህ በፊት በተሰጠው ጊዜ ቀጠሮ የሰራውን የምርመራ ስራ ለችሎቱ አቅርቧል።

በዚህም የምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን፣ በተጠርጣሪዎች እጅ የተገኘ ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ እንዲመረመር ለሚመለከተው አካል መላኩን እና አጠቃላይ የተደረገ የገንዘብ ዝውውርን ለማጣራት ለባንኮች ማስረጃ እንዲላክለት መጠየቁን ገልጿል።

መርማሪ ፖሊስ በሁለቱም መዝገቦች ቀሪ ስራዎችን አከናውኖ የምርመራ ማጣሪያ አድርጎ ለመቅረብ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።

በሁለቱም መዝገብ  የተሰየሙ የተጠርጣሪ ጠበቆችም ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ መፈቀድ የለበትም በማለት በመከራከር የተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት እንዲፈቀድ ጠይቀዋል።

መርማሪ ፖሊስም የተጠርጣሪዎች የዋስትና ጥያቄን በመቃወም ተከራክሯል።

የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ የተመለከተው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ  ፖሊስ በርካታ የምርመራ ስራ ማከናወኑን እና ማስረጃዎችን መሰብሰቡን መመልከቱን በዛሬው ቀጠሮ አብራርቷል።

ፖሊስ ቀሪ ከሚሰራው የምርመራ ስራ አኳያ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው መታመኑም ተገልጿል።

በዚህ መሰረት የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ሞላልኝ ሲሳይ እና አብርሃም ጌትነትን በሚመለከት ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረግ  ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ የ12 ቀን ጊዜ ፈቅዷል።

እነ ሰይፈ ተስፋዬ 5 ተጠርጣሪዎችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የ10  ቀናትን ተጨማሪ ጊዜን ለፖሊስ ፈቅዷል።

በዚሁ መዝገብ ተካተው የነበሩ ታደለ መንግስቱና አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ጊዜ መሰጠት አስፈላጊ አይደለም ሲል ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው በ15 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ አዟል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version