Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ኢ/ር ታከለ ኡማ በረመዳን ወር የመረዳዳት ባህላና ልምድ ከፍ ብሎ እንዲታይ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በረመዳን ወር የመረዳዳት ባህላና ልምድ ከፍ ብሎ እንዲታይ ጥሪ አቀረቡ።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በነገው እለት የሚጀምረውን የረመዳን ጾምን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም “ለመላው የእስልምና እምነት ተከታይ አባቶቼ፣ እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ እንኳን ለተከበረው የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ” ብለዋል።

“ይህ ወር የመንፈሳዊነት ልእልናን የምትጎናፀፉበት፣ የበረከት፣ የእዝነትና የመጣብን መከራ የሚያልፍበት ወር እንዲሆን እመኛለሁ” ሲሉም መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

ታላቁ የረመዳን ወር የመረዳዳት፣ የመተዛዘን እና የመተሳሰብ ወር ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ “አሁን ያለንበት ወቅት ደግሞ መረዳዳት እጅግ የሚያስፈልግበት ወቅት በመሆኑ እንደዚህ ቀደሙ የረመዳን ወር የመረዳዳት ባህላችሁና ልምዳችሁ ከፍ ብሎ ይታይ ዘንድ አደራ እላለሁ” ብለዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አጅክለውም “ውድ የሀገሬ ልጆች የመጣብንን መከራ እንድናልፍ ጥንቃቄ ሳይለየን፣ መመሪያዎችን ተግባራዊ እያደረግን ያለንን እያጋራን በአካላዊ መራራቅ ውስጥ የአብሮነትና አንድነት መንፈስን እያዳበርን እንድናሳልፈው ለማስታወስ እወዳለሁ” ብለዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

Exit mobile version