አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የዲጂታል ቢዝነስ አቅሞችን የሚለይ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ዛሬ እና ነገ በሚካሄደው አውደጥናት የዓለም ባንክ ፣ የዘርፉ ተዋንያን የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው ።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንደተናገሩት፥ የ አውደ ጥናቱ ዋና አላማ ዲጂታል ተወዳዳሪነትን በማሻሻል ሁሉንም ዜጋ በማካተት የዲጂታል ተጠቃሚ ማድረግ ነው ብለዋል ።
በተጨማሪም አውደጥናቱ የዲጂታል ቢዝነስን ሥነምህዳር ማስፋት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር እና ተጨማሪ የፋይናንስ ምንጭን ለማፈላለግ እንደሚረዳም ነው የተናገሩት።
የዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮግራም ዳይሬክተሩ ተሰማ ገዳ በበኩላቸው፥ ፕሮጀክቱ ለዲጂታል ዘርፍ ማደግ የሚጠቅሙ የህግ ማዕቀፎችን እንዲወጡ ለማድረግ እና የዲጂታል ትስስርን ለማጠናከር እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም የዲጂታል ቢዝነስ እና ኢንተርፕርነርሽፕን ማበረታታት ፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ላይ መስራት የፕሮጄክቱ ዋና ዋና ትኩረቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በፀጋዬ ወንደሰን