አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ አፈጻጸም የተሻሻለ ቢሆንም ክፍተቶች እንዳሉበት የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
በመንግሥታት ግንኙነት ጽንሰ-ሀሳብ እና በመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ አተገባበር ዙሪያ የፖሊሲ ማብራሪያ መድረክ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ስዩም መስፍን (ዶ/ር) እንዳሉት ፥ በፌደራልና በክልል መንግሥታት እንዲሁም በክልሎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመወሰን የወጣው “የመንግሥታት ግንኙነት ሥርዓት መወሰኛ አዋጅ 1231/2013” ሁለት ዓመት አልፎታል።
አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ ከዋለ በኋላም አፈጻጸሙን በተመለከተ ጥናት ተደርጓል ነው ያሉት።
በዚህም አዋጁ በመንግሥታት ግንኙነት ላይ መሻሻል ቢያሳይም የአፈጻጸም ክፍተቶች እንዳሉበት ጥናቱ ማሳየቱን ኢዜአ ዘግቧል።