አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 10 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና- አፍሪካን ትብብር በአዲስ ዕይታዎች በማዳበር ለማጠናከር ያለመ ሴሚናር በአዲስአበባ እየተካሄደ ነው፡፡
ሴሚናሩ እየተካሄደ ያለው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በስካይ ላይት ሆቴል እየተከበረ ባለበት ሁኔታ ነው፡፡
ሴሚናሩ “የቻይና አፍሪካ ትብብር አዳዲስ ዕይታዎችን በማጎልበት የቻይና አፍሪካን ማኅበረሰብ መፃዒ ዕድል መገንባት ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ይገኛል።
በሴሚናሩ ቻይና እና አፍሪካ በመነቃቃት እና በትብብር መንፈስ በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ሐሳቦች እና አፍሪካ ወደ ዝመና በምታደርገው ጉዞ ሊያጋጥሟት የሚችሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያስችሏት ሥልቶች ላይም ሐሳቦች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
እንዲሁም ቻይና እና አፍሪካ በመንግስት አስተዳደር ፣ በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ልማት ላይ የሚያደርጉትን የልምድ ልውውጥ ለማጠናከር እንደሚያግዝም ታምኖበታል።
የአፍሪካ ኅብረት የ2063 የልማት ግብ አንዱ አጀንዳ በሆነው እና የአፍሪካ ሀገራትን በመንገድ መሠረተ-ልማት ለማስተሳሰር በቻይና ዕውን የሚሆነውን “የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” ትገበራን ማፋጠን በሚቻልበት አግባብ ላይም ምክክር ይደረጋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም “በዓለምአቀፋዊ የዕድገት፣ የደኅንነት ፣ የሥልጣኔ ማዕቀፎች ላይ ብሎም በኅብረቱ የ2063 ዘጠኝ አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡
በዮናታን ዮሴፍ