አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከዓለምአቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ከዓለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ( አይ ኦ ኤም ) የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶ ዌንፎል ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው በድርጅቱ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ስላለው ግንኙነት እና ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።
በተለያዩ ግጭት ባለባቸው አገራት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞችን ለመደገፍ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ በርካታ ቁጥር ያላቸው የውጭ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድ እንዲሁም የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ያሉባት አገር እንደመሆኗ ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በጠንካራ ትብብር ትሰራለች ሲሉ ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ፍልሰት የደቀነውን ችግር ለመቅረፍ ድርጅቱ የሚሰራቸውን ስራዎች የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋግጠዋል።
የዓለምአቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ አቢባቶ ዌንፎል÷ ድርጅታቸው ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ለውጭ ፍልሰተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ዋና ተወካይዋ ኢትዮጵያ ልዩ ትኩረት የምንሰጣት አገር ናት ያሉ ሲሆን÷ የውጭ ፍልሰተኞችን በመቀበል ረገድም ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት እና ዓለምአቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት መካከል እያደገ የመጣ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው÷ በቀጣይም ከፍልሰት ጋር በተያያዙ ማዕቀፎች ትብብራቸው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።