አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 11 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የካናዳ ዓለም አቀፍ ልማት እና በፓሲፊክ ሀገራት የካናዳ ኢኮኖሚ ልማት ኤጀንሲ ተጠሪ ሚኒስትር ሃርጂት ሳጃን በኢትዮጵያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው።
ሚኒስትሩ ከፊታችን እሑድ ጀምሮ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብጽ እና ቻድ ለሳምንት የሚቆይ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል።
ከሚኒስትሩ ጋር የካናዳዋ ለንደን ዌስት የፓርላማ ተወካይ አሪዬሌ ካያባጋ በጉብኝቱ ይሳተፋሉ።
በሚኖራቸው ቆይታ ከመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር፥ በተለይም በምግብ ዋስትና፣ በኢኮኖሚ፣ በዓየር ንብረትና ብዝሃ ህይወት፣ በፆታ እኩልነትና ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም በሱዳን ሰብአዊ ቀውስ እና በቀጠናዊ ሁኔታ ይመክራሉ ተብሎም ነው የሚጠበቀው።
በኢትዮጵያ ቆይታቸውም በካናዳ መንግስት ድጋፍ የተሰሩ ፕሮጄክቶችን የሚጎበኙ ሲሆን፥ ከልማት እና የሰብአዊ ድጋፍ አጋሮች ጋር ይወያያሉ ነው የተባለው።
በተጨማሪም ከአፍሪካ ህብረት ባለስልጣናት ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም ተገልጿል።
በግብጽ ቆይታቸውም በአፍሪካ ልማት ባንክ አመታዊ ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ ይሆናል።

