አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በቀብሪበየህ ከተማ አስተዳደር እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ጎበኙ፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድና ልዑካቸው በጉብኝቱ በቀብሪበየህ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ የሚገኘውን የስፖርት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና ሌሎች የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን ተመልክተዋል፡፡
የስፖርት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣የመኝታ ክፍሎች፣ቤተ መፅሃፍት፣ሬስቶራንቶች፣የመዝናኛ ስፍራዎችና ሌሎች ዘመናዊ ህንጻዎችን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
በቀብሪበየህ ስፖርት ማሰልጠኛ ተቋሙ በዓይነቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በክልሉ የተገነባ ትልቅ ፐሮጄክት ስለመሆኑም ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እና ልዑካቸው በከተማዋ እየተሰራ ያለውን የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች ሂደትንም መጎብኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡