አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚኒሽነር ሌሊሴ ነሜ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ ሌሊሴ ነሜ በኢንቨስትመንት ዘርፉ እንቅስቃሴ፣ በተወሰዱ የሕግ ማሻሻያዎች፣ የአደረጃጀትና የአሰራር ለውጦች እና በዳያስፖራው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በግል እና የሽርክና አማራጮች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ከተዘጋጁ ዕድሎችና ማበረታቻዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሁሴን በበኩላቸው÷ የሀገር ኢኮኖሚ እንዲፋጠን እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲረጋገጥ በማድረግ ሂደት የዳያስፖራው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የዳያስፖራውን የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ለማሳደግም የተገኙ ውጤቶች የበለጠ በሚጠናከሩበትና ችግሮች በሚፈቱበት ዙሪያ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ምክክር መደረጉ ጠቀሜታው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡
የቀረበውን ገለጻ መነሻ በማድረግ ከዳያስፖራ ባለሃብቶች የተለያዩ ሃሳቦችና ጥያቄዎች ቀርበው ሰፊ ውይይት መደረጉንም የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡