አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 13 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 9 ወራት ከቱሪዝም ዘርፍ 3 ነጥብ 06 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው እንደገለጹት÷የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማስፋትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ ነው፡፡
በተለይም የውጭ ምንዛሪ ግኝትና የስራ ዕድሎችን በማስፋፋት የዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ከተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶች 3 ነጥብ 06 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡
774 ሺህ በላይ የውጪ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል ያሉት ስራ አስፈጻሚው÷ይህም በኮሮና ቫይረስና በጸጥታ ችግር ተቀዛቅዞ የቆየው የቱሪዝም እንቅስቃሴ መነቃቃቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
ነባርና አዳዲስ የቱሪዝም መስህቦችን ለይቶ በማጠናከር እንዲሁም የቱሪዝም መዳረሻዎች ላይ እሴት ጨምሮ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት ላይ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል፡፡
አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ የሆኑትን የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች (ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሀላላ ኬላ፣ ኮይሻ)፣የጅማ አባጂፋር ቤተ-መንግስትና የስንቀሌ የቆርኬዎች መጠለያን በተሟላ መልኩ ወደ ስራ ለማስገባት በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ተደራሽ የማስተዋወቂያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ የቱሪዝም ዘርፉን ይበልጥ ማማነቃቃትና የውጭ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ድንቅ መስህቦችን እንዲጎበኙ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
በመላኩ ገድፍ