Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የ9 ወራት የተቋማት አፈጻጸም ግምገማ ሚኒስትር ዴኤታዎችና የም/ቤት አባላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የተቋማት አፈጻጸም ግምገማ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በተገኙበት እየተካሄደ ነው።
 
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ባለፈው ሳምንት የሚኒስትሮች የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም መገምገሙ ይታወቃል።
 
በመድረኩ የዘጠኝ ወር የማክሮ ኢኮኖሚውን እና የሴክተሮች ልዩ አፈጻጸም ተገምግሟል።
 
የሚኒስትሮች የሩብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ሁለተኛው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ በመወያየት አቅጣጫ ማስቀመጡም ይታወቃል።
 
በዛሬው ዕለት ደግሞ የሚኒስትር ዴኤታዎችና የተቋማት የዘርፍ አፈጻጸም እየተገመገመ ይገኛል።
 
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፥ ባቀረቡት የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ሪፖርት የማክሮ ኢኮኖሚው አፈጻጸም የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በዚህም በየዘርፎቹ በበጀት ዓመቱ 7 ነጥብ 5 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችል አመላካች ውጤት መኖሩን ተናግረዋል።
 
በዚህ መድረክ በስድስት ወራት ግምገማ ወቅት የተቀመጡ አፈጻጸሞች ግምገማ የተቀመጡ አቅጣጫዎች አፈጻጸም እንደሚገመገም፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለም ፀሐይ ጳውሎስ አንስተዋል።
 
በመድረኩ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክርቤት አባላትና ቋሚ የኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ የተቋማት ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
Exit mobile version