Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በሐረሪ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ ፡፡
 
የሐረሪ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) የክልሉ የ100 ቀናት እቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።
 
አቶ ኦርዲን በድሪ በመድረኩ እንደተናገሩት÷ በክልሉ ባለፉት 100 ቀናት የተከናወኑ አበረታች ተግባራትን ማጠናከርና ክፍተቶችን መቅረፍ ይገባል ብለዋል።
 
የህዝቡን የኑሮ ውድነት ችግር ለማቃለል የተጀመሩ ስራዎችን ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
ለወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት መስጠትና ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው÷ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እንዲጎለብት መስራት እና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል።
 
መሰረተ ልማት ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ መንቀሳቀስ እና የክልሉን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስፋትና ዘርፉን ማጎልበት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
 
በክልሉ ሰላምና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እና ህገ ወጥ ግንባታን እና የመሬት ወረራን ለመከላከል አመራሩ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።
 
የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው÷ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የተጀመረው የፀረሙስና ትግል ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
 
የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱጀባር መሃመድ በበኩላቸው÷ የ100 ቀናት እቅዶቹ የክልሉ ህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እና ክፍተቶችን ለማረም ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
 
በክልሉ በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ ማስቻል እንደሚገባ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
 
የኑሮ ውድነት እንዲባባስ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ቆራጥ እና አስተማሪ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመው÷ አመራሩም የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል።
Exit mobile version