አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ ላይ የሚደረግ ተሳትፎን ማጠናከርና ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉ የኤኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
በሞሮኮ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ ላይ የሚሳተፉ ስምንት የኢትዮጵያ ስታርትአፖችና አይሲቲ ቢዝነሶች ሽኝት ተደረገላቸው።
ስታርት አፕ ድርጅቶቹ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባወጣው ውድድር የተመረጡ ሲሆኑ÷ በጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ድጋፍ እና ስፖንሰር ተደርገዋል።
እነዚህ ስታርትአፖች እና የአይሲቲ ቢዝነሶች ኢትዮጵያን በመወከል በዓለም አቀፉ የቴክኖሎጂ አውደ-ርዕይ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን÷ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኤኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያን ተሞክሮ በአለምአቀፉ የቴክኖሎጂ አወደ ርዕይ ለማሳየት የተፈጠረው እድል መልካም የሚባል ጅምር ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም እንዲህ ያሉ ተሳትፎችን በይበልጥ ማጠናከርና ማስፋት ያስፈልጋል ማለታቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡