Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 5 ሚሊየን ዜጎችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ 5 ሚሊየን ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ዛሬ ይፋ ሆኗል።

“በጎ ፈቃድ ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚተገበረውን ፕሮጀክት ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል የአምስት ዓመት ስምምነት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ባለስልጣን እና ‘አሊያንስ ኬር ፎር ናው’ የተባለ አጋር ድርጅት ተፈራርመዋል።

በሁሉም ክልሎች የሚተገበረው ፕሮጀክት 5 ሚሊየን ያህል ዜጎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 5 ሚሊየን አገር በቀል በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙም ተጠቁሟል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ተሰማርቷል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማጠናከር እንዲሁም የአገር ውስጥ ሰፊ አቅምን በመጠቀም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተጎዱ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ስራዎች በቅንጅት እየተሰሩ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሐ-ግብሮችን ከሌሎች ኢኒሼቲቮች ጋር በማስተሳሰር ለመተግበር ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሐ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ አጋር ድርጅቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ2014ዓ. ም የክረምት መርሐ-ግብር ከ24 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ መሳተፋቸው በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል።

Exit mobile version