Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በአማራ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ዞኖችና ከተሞችን ለማቋቋምና ለመገንባት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን 7 ዞኖችና 3 ሪጂዮፖሊታን ከተሞችን መልሶ ለማቋቋምና ለመገንባት ከ522 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ገለፀ።

ከተለያዩ አከባቢዎች ተፈናቅለው በክልሉ የሚገኙ ከ1 ነጥብ 1ሚሊየን በላይ ህዝብ ለከፍተኛ ችግር ተጋላጭ ሆነው የዕለት ደራሽ ምግብና መጠለያ ይፈልጋሉም ብሏል።

አሁን ላይ በክልሉ ወደ 11ነጥብ 4 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጫና ውስጥ እንደሚገኙም ተጠቅሷል፡፡

ከመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ጋር በተያያዘ ክልሉ አዲስ ጥናት ማስጠናቱንም ነው ቢሮው የገለጸው፡፡

በገንዘብ ቢሮ አዘጋጅነት የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመታዊ የአጋርነት ምክክር በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የክልሉ የገንዘብ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ደመቀ ቦሩ (ዶ/ር) ÷በክልሉ ያለው ማህበራዊ ችግር ከፍተኛ በመሆኑ የሁሉን ባለድርሻ አካላት ገንዘብና እውቀት ማስተባበር ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወደ 7 ቢሊየን ብር በሚገመት ከ374 በላይ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከክልሉ ጋር ስምምነት መፈፀማቸውንና ወደ ተግባር መግባታቸውን አንስተዋል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት የገንዘብና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አለምነሽ ዋጋዬ በበኩላቸው ÷የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ስምምነት ያደረጓቸውን ፕሮጀክቶች በሀላፊነት እንዲፈፅሙ ጠይቀዋል።

የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት በክልሉ የልማት ስራዎችን እየሰሩ የሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ይበልጥ ስራቸውን ሊያጠናክሩ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በታሪኩ ለገሰ

Exit mobile version