አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችን ያካተተ ልዑክ የአፍሪካ አሕጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና ልዩ የሚኒስትሮች ስብሰባን በኬንያ ናይሮቢ እየተሳተፈ ነው፡፡
በስብሰባው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እየተሳተፉ ሲሆን÷ የነጻ ንግድ ቀጠናው አባል ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮችም በስብሰባው ታድመዋል፡፡
በስብሰባው ቀዳሚ አጀንዳ “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና (AfCFTA)” ትግበራን ለማሳለጥ የግሉ ዘርፍ ሚና በተመለከተ ሪፖርቶች ቀርበው ውይይቶችን በማድረግ ተጀምሯል፡፡
በቀጣይ ውሎውም “የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራ የደረሰበትና ያጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም እስከ አሁን በተደረጉ ድርድሮች መቋጫ ያላገኙ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጥ የቀጣይ ቀናት የስብሰባው የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ተብሏል፡፡
እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት የዓመቱ መሪ ቃል”የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ትግበራን ማፋጠን” እንደመሆኑ የስምምነቱን ትግበራ ለማሳለጥ ፍኖተ ካርታና ዝርዝር የትግበራ ሰንጠረዥ ዝግጅት ዙሪያ ምክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአፍሪካ አህጉራዊ የነጻ ንግድ ቀጣና ልዩ የሚኒስትሮች ስብሰባ እስከ ነገ እንደሚቀጥል መገለጹን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡