Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በመጨረሻው ሩብ ዓመት የሚፈጸሙ ግዢዎችን የሚያስቀር አሰራር ሊተገበር ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግሥት ተቋማት በመጨረሻው ሩብ ዓመት የሚፈጸሙ ግዢዎችን ለማስቀረት የሚረዳ አሰራር ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ እንዳሉት ÷ተቋማት የሚፈጽሙት ግዢ ባመዛኙ ያልታቀደና በአራተኛው ሩብ ዓመት ላይ ያተኮረ ነው።

በዚህ ወቅት የሚፈጸሙ ግዢዎች ለመልካም አስተዳደር ችግሮች የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነና “90 በመቶ የሚሆነው የኦዲተሮች ግኝት ተቋማት በመጨረሻው ሩብ ዓመት ከሚፈጸሙት ጋር የተያያዘ ነው” ብለዋል።

ተቋማት ምን መግዛት አለባቸው፣ መቼ ነው የሚገዛው፣ ከየት ነው የሚገዛው፣ የጨረታ ሂደቱ እንዴት ይሆናል ፣ በሚለው ዙሪያ አቅዶ በመስራት በኩል ሰፊ ክፍተት እንደሚስተዋል ነው ያስረዱት።

ከስልጠናዎች ጋር በተያያዘም ተቋማት የስልጠና መርሐ ግብሮችን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ወይም በሐምሌ፣ ነሐሴና መስከረም የዝግጅት ምዕራፍ ማካሄድ ያለባቸው ቢሆንም ይሄ እየተተገበረ አይደለም ብለዋል።

65 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቷ በጀት የሚውለው ግዢ ላይ መሆኑን ጠቁመው÷ በጀቱ በዕቅድ ላይ ተመስርቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለ በሀገርና ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በመጨረሻው ሩብ ዓመት ተቋማት የሚገዙበት ሥርዓት ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ እንደማይኖር የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ÷ ያልታቀዱ ግዢዎችን ለማስቀረት የመንግሥት ኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የኤሌክትሮኒክ ግዢ ሥርዓቱም በ2016 ዓ.ም በሁሉም የፌደራል ተቋማት እንደሚተገበር አስረድተዋል፡፡

Exit mobile version