Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ከኦራክልና ቪዛ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከኦራክል እና ቪዛ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ፡፡

በሞሮኮ ማራክሽ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው  “የጂአይቴክስ” አፍሪካ ሁነት ከመላው ዓለም የተውጣጡ ታዋቂ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና ጀማሪ ቴክኖሎጂስቶች እየተሳተፉ ነው፡፡

በሁነቱ አውደ ርዕዮችና አውደ ጥናቶች እየተካሄዱ ሲሆን÷የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸውም እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

ሚኒስትሩና ልዑካቸው ከሁነቱ፣ አውደርዕዮችና የስማርት አፍሪካ አውደ ጥናት ተሳትፏቸው ጎን ለጎን ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን እያካሄዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በዛሬው እለትም በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷ ከኦራክል እና ከቪዛ ኩባንያዎች የስራ ኃላፊዎች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

ሚኒስትሩ በውይይታቸውም÷በኢትዮጵያ እየተከናወነ ሰላለው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሂደት ለሥራ ኃላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡

መሰረቱን አሜሪካ ቴክሳስ ያደረገው ዓለም አቀፉ የኦራክል ኩባንያ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ ላይ የተሰማራ የቴክኖሎጂ ድርጅት ሲሆን÷በዳታቤዝና ሶፍትዌሮች ልማት እንዲሁም አገልግሎት፣ በክላውድ አገልግሎት እና መሰረተ ልማት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው ተብሏል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያም በርካታ የዳታቤዝና የሶፍትዌር ልማቶች ላይ ፕሮጀክቶችን እያለማና ባለሙያዎችንም እያፈራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡

የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው÷በኢትዮጵያ የዲጂታል ገበያ ለመሳተፍና አገራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጥረቱን ለማገዝ ስትራቲጂካዊ ጥምረት በመፍጠር በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።

በተጨማም ሚኒስትሩ  ዋና መሰሪያ ቤቱን አሜሪካ ሳንፍራንሲስኮ ካደረገው ከቪዛ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ  ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የቪዛ ኩባንያ የኤሊክትሮኒክ ክፍያዎችንና የገንዘብ ዝውውሮችን የሚያቀላጥፍ ሲሆን÷ በኢትዮጵያም ከባንኮች ጋር በመጣመር ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍና አገራዊ የክፍያ ስራዎችን ለማሳለጥ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

የኩባንያው ኃላፊዎች በበኩላቸው÷የሞባይል ክፍያን ለማስፋፋት በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ኩባንያው የፈጠራ ሰራዎችን ለመደገፍ እና  ከዕለት ወደ ዕለተ የበለጠ እየተከፈተ በመጣው የኢትዮጵያ የዲጂታል ገበያ እድል ውሰጥ ለመሳተፍ  እቅድ እንዳለው አመላክተዋል፡፡

 

Exit mobile version