አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአንድ ቢሊዮን ዓመት እድሜ ያለው ፍጥረት ቅሪተ አካል በሰሜን አውስትራሊያ አለቶች ላይ መገኘቱን ሳይንቲስቶች ገለፁ፡፡
የቅሪተ አካሉ ግኝት ዓለም ስለ ሰው ልጅ አመጣጥ ያለውን ግንዛቤ ሊቀይር ይችላል ነው የተባለው፡፡
ፕሮቶስትሮል ባዮታ የተባለው ይህ ቅሪት አካል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ እና ኢዩካርዮትስ በመባል የሚታወቁት ፍጥረታት አካል መሆኑ ታውቋል፡፡
በአውስትራሊያ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ቤንጃሚን ኒተርሺም÷እነዚህ ጥንታዊ ፍጥረታት በባህር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ እና የመሬት ስነ ምህዳርን የፈጠሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ሰሜናዊ አውስትራሊያ ከመካከለኛው የእድሜ ዘመን ጀምሮ የነበሩ አለቶች የሚገኝበት ስፍራ ሲሆን÷ ቀደም ሲል የአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ አውስትራሊያ እና የጀርመን ሳይንቲስቶች በአካባቢው ላይ ምርምራ ሲያደርጉ መቆየታቸውም ተነግሯል፡፡
የፕሮቶስትሮል ባዮታ የተባለው ቅሬተ አካል በአውስትራሊያ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ለ10 ዓመት ጥናት ሲደረግበት የቆየ ሲሆን÷ የግኝቱ ውጤት በዛሬው እለት ይፋ መሆኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡