አዲስ አበባ፣ ሰኔ 01፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 801 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ሆኖ የተዘጋጀው የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡
6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን 24ኛ መደበኛ ስብሰባ እየተካሄደ ነው፡፡
ለም/ቤቱ በቀረበው የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ላይም የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ማብራሪያ እየሰጡ ነው፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባካሄደው 21ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2016 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ረቂቅ የበጀት አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
የ2016 በጀት በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ የተቀመጡ ግቦችን ታሳቢ በማድረግ፣ የሀገር ደህንነት ከማስጠበቅ፣ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጐችን ከመርዳት፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው የወደሙ መሰረተ ልማቶች መልሶ ከማቋቋም፣ በቀጣይ ሊኖር የሚችለውን የማህበራዊና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን አቅጣጫዎችና ዓላማዎች ከማሳካት አኳያ የተቃኘ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ረቂቅ በጀቱ የ2016 – 2020 የመካከለኛ ዘመን የማክሮ ኢኮኖሚ እና የፊሲካል ማዕቀፍን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በዚሁ መሰረት ለፌደራል መንግስት መደበኛ ወጪዎች ብር 369 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች ብር 203 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ ብር 214 ነጥብ 07 ቢሊየን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 14 ቢሊየን ብር በጠቅላላው 801 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ሆኖ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በረቂቅ በጀቱ ላይ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።