Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ማዘመን የሚያስችሉ በርካታ የለውጥ ሥራዎች ተሰርተዋል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ማዘመን የሚያስችሉ በርካታ የለውጥ ሥራዎች መሰራታቸውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

በቢሾፍቱ ከተማ በተካሄደው “የሥራ ባህልን መለወጥና የዕይታ አድማስን ማስፋት” የውይይት መድረክ የተሳተፉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና ሌሎች አካላት የአየር ኃይል የለውጥ ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ በተቋሙ የተወሰደው የለውጥ እርምጃ አገርን በችግር ውስጥም መገንባት እንደሚቻል ያሳየ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ አየር ኃይልም አስተማማኝ የሰው ኃይልና ዘመናዊ ትጥቅ እንዲኖር በማድረግ እንዲሁም ተቋሙ ፅዱና ማራኪ እንዲሆን ያስቻለ የተለያዩ የለውጥ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።

የሰራዊቱን አቅም በመገንባት ተቋሙንም ከማንኛውም የፖለቲካ፣ የኃይማኖትና የብሔር አስተሳሰብ ነፃና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኩራት እንዲሆን ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት ያሉት ሌተናል ጄነራል ይልማ÷ ሀገሪቷም ያላትን ታሪክ፣ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት ታሳቢ በማድረግ በአየር ኃይል ላይ በርካታ የለውጥ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

በአየር ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና የ5ኛ አየር ምድብ አዛዥ ኮሎኔል ብሩክ ሰይፉ÷ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ በመንደፍ በተቋሙ ላይ ውጤታማ የልማት ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

በዚህም በሰው ኃይልና በዘመናዊ ትጥቅ በማደራጀት የኢትዮጵያን አየር ክልል ማስጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ተቋም መገንባት እንደተቻለ መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version