አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ ኢትዮጵያን ሊጎበኙ ቀን መቅጠራቸው ተገለጸ፡፡
የሉላ የኢትዮጵያ ጉብኝት በዋናነት ብራዚል ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የንግድና ዲፕሎማሲ ግንኙነቷን ለማጠናከር የወጠነችው ዓላማ አካል መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ኦ ግሎቦ የተሠኘው የሀገሪቷ ጋዜጣ እንዳስነበበው ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ አንጎላን ፣ ሞዛምቢክን ፣ ሴኔጋልን ፣ ጋናን ፣ ናይጄሪያን እና ሳዖቶሜና ፕሪንሲፔን ለመጎብኘት አቅደዋል፡፡
በተጨማሪም ኤምባሲያቸውን በሴራሊዮን እንደሚከፍቱ እና በሩዋንዳ ተጨማሪ ውክልና እንዲኖራቸው እንደሚሠሩ ተጠቁሟል፡፡
ሉ ዳ ሲልቫ በአኅጉረ-አፍሪካ በሁለት ዙር በ23 ሀገራት ይፋዊ የሥራ ጉብኝት የሚኖራቸው ሲሆን፥ በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጃዬር ቦልሶናሮ አስተዳደር ችላ የተባለችውን አፍሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማስተካከል መሆኑንም ጋዜጣውን ዋቢ አድርጎ ብሉምበርግ ዘግቧል።
አሁን ላይ ብራዚል ከአፍሪካ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከማደስ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ትስስሯን ለማጠናከር ማቀዷም እየተነገረ ነው፡፡
ብራዚል የደቡብ – ደቡብ ትሥሥር አጀንዳዋን ዕውን ለማድረግ በአፍሪካ ያለውን የንግድ እና ቢዝነስ ዐቅም ለመጠቀም እና ከያዘችው አጀንዳ ጎን ለጎን የማስኬድ እቅድ እንዳላትም ተጠቅሷል።
ሉላ የመጀመሪያ ዙር የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በነሐሤ ወር መጀመሪያ እንደሚጀምሩም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን ባለስልጣናት ዋቢ ያደረገው ዘገባው ያመላክታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በየካቲት ወር በሚካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ላይ በመገኘት አጋጣሚውን በሁለተኛው ዙር ጉብኝታቸው ለመጠቀም ማሰባቸውም ተገልጿል።