Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

ዓለም አቀፍ የደም ለጋሾች ቀን እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 7 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፍ ደም ለጋሾች ቀን ”ደም እንለግስ ፤ ሕይወት እናጋራ ፤ ዘወትር እናጋራ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ ነው፡፡

በአከባበር ሥነ -ሥርዓቱ ላይ የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ጤናዬ ደምሴ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ፈቃዱ ረጋሳ እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ወ/ሮ ጤናዬ ደምሴ ፥ የደም ለጋሾች ቀን ከስጦታዎች ሁሉ ውድ የሆነውን የደም ስጦታ የሚያበርክቱ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ለማመስገን በየዓመቱ ሰኔ 7 ቀን የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቀኑ የማይተካውን የሕይወት ስጦታ የሚሰጡ መደበኛ ደም ለጋሾችን እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ሕይወትን እንዲታደጉ ለማበረታታት በማለም እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡

በቂ ደም ሰብስቦ ለጤና ተቋማት ተደራሽ በማድረግ የሰውን ሕይወት በመታደግ ረገድ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት የሚስተዋለውን የደም እጥረት ለመቅረፍ የተቀናጀ የደም ልገሳ መርሐ- ግብር ማካሄድ አስፈላጊ እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ዜጎች በሀገሪቱ የሚስተዋለውን የደም እጥረት ግምት ውስጥ በማስገባት ደም እንዲለግሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ባለሙያዎች ከደም ማሰባሰብ፣ መመርመርና ደኅንነቱ የተረጋገጠ ደም ለጤና ተቋማት በወቅቱ እንዲደርስ በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

በመርሐ -ግብሩ በመላ ሀገሪቱ ለበርካታ ጊዜያት ደም ለለገሱ ዜጎች እውቅና ተሰጥቷል።

በመላኩ ገድፍ እና ሳራ መኮንን

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
Exit mobile version