አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)አገራት የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ይዞት የመጣውን እድል ለሰላም ግንባታና ኢኮኖሚ ትስስር መጠቀም ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች ገለጹ፡፡
ሜክሲኮ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ቱርክና አውስትራሊያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 2013 በጋራ በመሆን ‘ሚክታ’ የተሰኘ ቡድን መመስረታቸው ይታወቃል፡፡
ቡድኑ በዋናነት በአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚመራ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ የግንኙነት መርሆችን በአከበረ መልኩ ዓለም አቀፋዊ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታትና የአገራቱን የጋራ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ ይሰራል፡፡
በዛሬው እለትም በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ ኤምባሲ አዘጋጅነት ”የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት ለሁሉ አቀፍ ተግዳሮቶች ምላሽ ” በሚል መሪ ሃሳብ ሴሜናር ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ በዋናነት ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን የተመለከተ ልምድ ልውውጥና ምክክር የተደረገ ሲሆን÷ ከኢፌዴሪ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት የተውጣጡ አካላት ተሳትፈዋል።
በኢትዮጵያ የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ባስራ ባስኑር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት÷ አምስቱ ሀገራት ዓለም አቀፍ ልማትና እድገት እንዲሁም በአስተዳደራዊና ሁሉን አቀፍ ለውጥ ውስጥ በጥምረት ሲሳተፉ የቆዩ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2023 በሀገራቱ ትብብር ውስጥ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት ትልቅ ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለኢኮኖሚ ግንባታ እንዲሁም ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሰጠቸውን ትኩረት አድንቀው÷ ከዚህ አኳያ ሴሚናሩ በኢትዮጵያ እንዲካሄድ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሜክሲኮ አምባሳደር ቪክቶር ትሬቪኖ በበኩላቸው ÷የ ‘ሚክታ’ አባል አገራት የተለያዩ የዓለም ክፍልን እንደመወከላቸው የዲጂታል ዘርፉ ለዓለም ሰላም በጎ ሚና እንዲጫወት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ሲዮኬ በበኩላቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ መስፋፋት በተለይ ሰፊ የማደግ አቅም ላላቸው የአፍሪካ አገራት አድል ይዞ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ቤርክ ባራን÷በኢትዮጵያ ለዲጂታል ዘርፍ እድገት የሚሆን ምቹ እድል መኖሩን ጠቅሰው፤ ሴሚናሩ በኢትዮጵያ መካሄዱ ይህን ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የዲጂታል አካታችነትን ለማረጋገጥ የዘርፉ ተቋማት በቅንጀት ሊሰሩ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት ናቸው፡፡