Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የኮኬይን ዕፅ የያዘ የውጭ ሀገር ዜጋን አስመልጠዋል ተብለው የተከሰሱ 2 የፌዴራል ፖሊስ ዋና ኢንስፔክተሮች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኮኬይን ዕፅ የያዘን የውጭ ሀገር ዜጋን አስመልጠዋል ተብለው የተከሰሱ ሁለት የፌዴራል ፖሊስ ዋና ኢንስፔክተሮች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸውን ከሰባት በላይ የሰው ምስክሮችን ቃል እና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ነው ሁለት ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን የሰጠው።

ፍርድ ቤቱ በዚሁ መዝገብ የተካተተ ሌላ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ የሆነ ተከሳሽ ላይ ደግሞ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።

በቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው ተከሳሾች የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ሥራ ላይ ተመድበው ሲሰሩ ነበር የተባሉት ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ባሌማ እና ዋና ኢንስፔክተር ጌታነህ ሞገስ ናቸው።

ሌላኛው ጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠበት ተከሳሽ ደግሞ የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ ይባላል።

ከዚህ በፊት በነበረ ቀጠሮ በዚሁ የክስ መዝገብ 3ኛ ተከሳሽነት ተካቶ የነበረው ዳንዔል ተሥፋ የማነ የተባለ (ሹፌር) ተከሳሽን በሚመለከት በፖሊስ ተፈልጎ ባለመገኘቱና በጋዜጣ ጥሪ ተደርጎለት ሳይቀርብ በመቅረቱ ምክንያት በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስ ክሱ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ ላይ በጥር 26 ቀን 2015 ዓ/ም በተከሳሾቹ አቅርቦት የነበረው ክስ ላይ እንደሚያመላክተው÷ በታህሣሥ 20 ቀን 2015 ከምሽቱ 1 ሠዓት ከ35 ደቂቃ ላይ ከብራዚል ሳኦፓሎ ተነስቶ አዲስ አበባ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ ትራንዚት በማድረግ ወደ ጆሃንስበርግ የሚሄድ ብራዚላዊ ዜግነት ያለውን ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የሚባል 4ኛ ተከሳሽ “ሴንትራል ጌም” ተብሎ በሚጠራው የፍተሻ ጣቢያ ላይ ሲፈተሽ እንዳይዘዋወርና ጥቅም ላይ እንዳይውል የተከተከለ 27 ነጥብ 65 ኪሎ ግራም ኮኬይን ዕፅ በሻንጣው ውስጥ ይዞ እጅ ከፍንጅ ተገኝቷል፡፡

ይህን ተከትሎም 1ኛ ተከሳሽ ከሌሎች የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ሠራተኞች ጋር በመሆን ዕፁን አስቆጥሮ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር ከእነ ዕፁ 4ኛተከሳሽን በቁጥጥር ሥር አውለዋል፡፡

በመቀጠል 4ኛ ተከሳሽ የሆነውን የውጭ ዜጋ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አደንዛዥ ዕፅ መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የፀረ ፈንጅና አደንዛዥ ዕፅ ቁጥጥር መምሪያ ማስረከብ ሲገባቸው ዕፁንና ግለሰቡን አሳድረው ታኅሣሥ 21 ቀን 2015 ከጠዋቱ 2 ሠዓት ላይ 1ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ግለሰቡን ከእነ ዕፁ ጭነው ወደ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ በመውሰድ ላልተያዘ 3ኛ ተከሳሽ ዕፁንና ግለሰቡን በማስተላለፍ 3ኛ ተከሳሽም በሚያሽከረክረው “ቪትዝ” መኪና ውስጥ በማስገባት ግለሰቡ እንዲሸሽ ተደርጓል ሲል ዐቃቤ ህግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

እንደ አጠቃላይ ተከሳሾቹ በቀረባቸው ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ላይ ዐቃቤ ህግ ከሰባት በላይ የሰው ምስክር እና ማስረጃ በተለያዩ ቀናት አቅርቦ አሰምቷል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በዐቃቤ ህግ የቀረበ የሰው ምስክር ቃል እና ማስረጃን መርምሮ ነው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች እንዲከላከሉ በዛሬው ቀጠሮ ብይን የተሰጠው።

ሌላኛው የብራዚል ዜግነት ያለው ክርስቲያን ዲ ኦሊቬራ ማርቲኒስ የተባለ 4ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ በቀረበበት ክስ ላይ ወንጀሉን መፈጸሙ መረጋገጡን ገልጾ በሌለበት የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎበታል።

1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ለሐምሌ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

Exit mobile version