Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

የአርቲስት ዓሊ ብራ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተገነባው የክብር ዶክተር አርቲስት ዓሊ ብራ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የገንዝብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልቀድር፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች የአርቲስቱ ቤተሰቦችና ወደጆች ተገኝተዋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ÷ አርቲስት ዓሊ ብራ በሥራዎቹ ስለአንድነት፣ አብሮነት፣ ፍቅር፣ ሰላምና ፍትሕ በማቀንቀን ዘመን የሚሻገር ዐሻራ ትቶ አልፏል ብለዋል፡፡

የመታሰቢያ ሐውልቱ ይህን የአርቲስቱን በጎ ሥራ የሚዘክር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከንቲባ አዳች በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የክቡር ዶክተር ዓሊ ብራ÷ “አምላክ ነው ወይንስ ሰው ሕግን ያጣመመው? የአንድ እናት ልጆች ነን የሚለያየን ማንነው?” በማለት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሕዝቦች መካከል እንዲሰፍን ያቀነቀነ ሀገር ወዳድ ጀግና ነበር ብለዋል፡፡

ለክብር ዶክተር ዓሊ ብራ መታሰቢያ ሐውልት ሲቆምለት÷ ትውልዱ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፤ ከግለኝነት ይልቅ የሀገርና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደምን እንዲማርበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

አቶ አሕመድ ሽዴ አርቲስቱ በሥራዎቹ የሕዝቦች መስተጋብር እንዲጠናከር ማድረጉን አንስተዋል፡፡

የአርቲስት ዓሊ ብራ የቅርብ ጓደኛ መሐመድ ቆጴ በበኩላቸው አርቲስቱ ለኦሮሞ ብሎም ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡

የመታሰቢያ ሐውልቱ የአርቲስት ዓሊ ቢራን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሚናው የጎላ መሆኑንንም ጠቅሰዋል፡፡

ከምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በኋላም የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ተከናውኗል።

ከ50 ዓመታት በላይ በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ዐሻራ ትቶ ያለፈው አርቲስት ዓሊ ብራ ባደረበት ህመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ÷ ጥቅምት 27 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል፡፡

በበረከት ተካልኝ

Exit mobile version