አዲስ አበባ፣ ሰኔ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ)አሲዳማ አፈርን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከም የማዕድን እና የግብርና ሚኒስቴር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ(ኢ/ር)ና የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በአሲዳማ አፈር ላይ ያለውን ችግር በፍጥነት ለመፍታት ተወያይተዋል፡፡
የሚኒስቴሮቹ የስራ ሃላፊዎችም በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን አሲዳማ አፈር በኖራ ድንጋይ ለማከም የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅርው ስራ ጀምረዋል፡፡
አሲዳማ አፈር በኢትዮጵያ እየተስፋፋ በመምጣቱ ምርትና ምርታማነት በአንዳንድ አካባቢዎች እየቀነሰ መምጣጡ ተገልጿል፡፡
በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በደቡብ ክልሎች የአሲዳማ አፈር ተጠቂዎች መሆናቸው ከማዕድን ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በአጠቃላይም በኢትዮጵያ ከ3 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄከታር መሬት በከፍተኛ ሁኔታ በአሲዳማ አፈር ተጠቅቷል ነው የተባለው፡፡