አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጃን ሜዳ አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ግርግር በስድስት ሰዎች ላይ ቀላል እንዲሁም በአንድ ግለሰብ ላይ መካከለኛ ጉዳት መድረሱን የአዲስ አበባ ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ጉዳቱ ያጋጠመው በተከሰተ መገፋፋት መሆን ፓሊስ ገልጿል።
የንግዱ ስርዓቱ ህጋዊ መንገዱን ተከትሎ እንዲከናወን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፤ ከደንብ ማስከበር አገልግሎት እና ከሌሎች ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ሆኖም በዛሬው ዕለት ግብይቱ በመከናወን ላይ እንዳለ የተፈጠረውን ረብሻ ተከትሎ በተከሰተ መገፋፋት ስድስት ሰዎች ላይ ቀላል እንዲሁም በአንድ ግለሰብ ላይ መካከለኛ ጉዳት ማጋጠሙን በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የፈረንሳይ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ሰለሞን ገ/ማርያም ገልፀዋል፡፡
ከተጎጂዎቹ መካካል ስድስቱ ህክምና አግኝተው ከሆስፒታሉ መውጣታቸውንና አንደኛው ተጎጂ ህክምናውን እየተከታተለ እንደሚገኝ ኃላፊው ተናግረዋል።
በአካባቢው በተፈጠረው ግርግር ሁለት ሰዎች ሞተዋል ተብሎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የተሰራጨው መረጃ ሐሰት መሆኑን ምክትል ኮማንደሩ ተናግረው ፖሊስ አጋጥሞ የነበረውን እረብሻ በቀላሉ ተቆጣጥሮ ግብይቱ እንዲቀጥል መደረጉን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

