Site icon Welcome to Fana Media Corporation S.C

በትግራይ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎትን ወደ ነበረበት ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በክልሉ በየደረጃው የሚገኙ የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በሙሉ አቅም ወደስራ እንዲገቡ÷ አዳዲስ በወጡ የትራንስፖርት ዘርፍ ሕጎችና አሰራሮች፣ በሎጂስቲክስ ጽንሰ ሐሳቦችና በስነ ልቦና ዝግጅት ላይ የሁለት ቀናት ስልጠና በመቐለ እየተሰጠ ነው፡፡

በርካታ ጉድለት የሚስተዋልበትን የትግራይ ክልል የትራንስፖርት አገልግሎት ለማስተካከል ሚኒስቴሩ የጀመራቸውን ድጋፎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በክልሉ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ ለመስጠት ያሳዩት ተነሳሽነት አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም በቁርጠኝነት በመስራት የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት እንደሚስፈልግ አመላክተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ካቢኔ ሴክሬታሪያት መሠረተ ልማት ኃላፊ ያለም ፀጋይ÷ በክልሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ያለውን አቅምና የሚኒስቴሩን ድጋፍ በአግባቡ በመጠቀም ሁላችንም የሚጠበቅብንን ድርሻ በአግባቡ ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ታደለ መንግስቱ በበኩላቸው÷ የክልሉን የትራንስፖርት አገልግሎት በተሟላ ሁኔታ ለማስጀመር የግብአት እጥረት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታትም በጋራ መስራት እንደሚገባ ነው በአጽንኦት የገለጹት፡፡

ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ስልጠና ላይ÷ ከክልል፣ ከዞንና ወረዳወች የትራንስፖርት ቢሮዎች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡

በዮሐንስ ደርበው

 

 

Exit mobile version